Gudumaale

   Sidaamu Daga Budu Battala
Connecting Sidama People

የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ከድንበር/ወሰን ግጭት ጋር መቀላልቀ አግባብ አይደለም፤ መፍትሄም አይሆንም!!!
 

የሲዳማ ጥያቄ የክልልነት መብት ጥያቄ እንጂ የወሰን ወይም የድንበር ይከበርልኝ ጥያቄ አይደለም። የሲዳማ ጥያቄ ሕገ-መንግሥታዊ መብትን የማስከበር ጥያቄ ነው። (አንቀጽ 47(2)፥ አንቀጽ 39(3)ን ይመልከቱ።)

ይህንን ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ ህጋዊነት ባለው መንገድ መጠየቅ የተጀመረው ዛሬ ሳይሆን ከ 1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ነው።

በተለይ እኤአ ከ2000 ጀምሮ ይህንን ጥያቄ የደቡብ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሕገ-መንግሥት እና የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት (አንቀጽ 39(4)) በሚፈቅደውና በሚያስቀምጠው ሥነሥርዓት መሠረት በዞኑ ምክር ቤት በ 100% ድምፅ አስወስኖ ጥያቄውን ለደቡብ ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት እና በኋላም ለኢትዮጵያ ፌደሬሽን ምክር ቤት አቅርቦ ሕዝቡ በሬፈሬንደም የራሱን ዕድል በሕግ አግባብ በራሱ እንዲወስን ቢጠይቅም ምንም መልስ እንዳልተሰጠው ይታወቃል። የሁለቱም ምክር ቤቶች የዚህን ጥያቄ መዝገብ እስከዛሬ ድረስ ይዘው መልስ ሳይሰጡት እንደቆዩ ሁሉም ኢሕአዴጋዊ አመራር (ምናልባትም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ሳይጨምር) ያውቀዋል።

የወቅቱ የብዙዎቹ (ቅን) ሰዎች ፍርሃት "የሲዳማን መብት ካከበርን የጋሞን፥ የወላይታን፥ የጉራጌን፥ የከንባታን፥ የሃዲያን፥ የከፋን፥ የዳውሮን፥ የጎፋን፥ ወዘተ ጥያቄስ ምን ልናደርገው ነው?" የሚል ነበር።

ጥያቄው ሕገ-መንግሥታዊ መብት ከሆነ መደረግ የሚገባው፥ ጥያቄዎቹን ተራ በተራ እየመለሱ መልሶቹ ለሚያስከትሏቸው ጥያቄዎች ደግሞ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት እየተዘጋጁ ልብን አስፍቶ መጠበቅ ነበር።

ይሄን ከማድረግ ይልቅ "አይ ይሄ አካሄድ ክልሉን ያፈርሳል!" እያሉ የሌለ ፍርሃት ማራገብ የደኢሕዴን ትልቁ ስህተት ነበር። (አንደኛ፣ መብት ስለተከበረ ክልልም ሆነ አገር አይፈርስም። የት ይሄዳል፥ ምንስ ይሆናል?!? ሁለተኛ፣ ይሄ ክልል እኮ ፍፁም አርቲፊሻል፥ በዘፈቀደ አሰራር ለወያኔ አገዛዝ እንዲመች ብቻ የተፈጠረ፥ የሕወኅት ስሪት ነው። ቢፈርስስ? "ደቡብ ብሎ አቅጣጫ እንጂ ሕዝብ የለም!" የሚለውን አባባል ልብ ይሏል።)

የሲዳማ ሕዝብ ይሄን ጥያቄ በሕገ-መንግሥታዊ የዳኝነት ሂደት እንዲመለስለት ከመጠየቅ አልፎ፥ በየፖለቲካ መድረኩ ያላነሳበት ዓመት አልነበረም። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፥ አቶ ሃርቃ ሃሮዬን ከፍትህ ሚኒስትርነት ያስነሳው የዚህን ጥያቄ ሕገ-መንግሥታዊነት በደኢሕዴን መድረክ ላይ ሲቀርብለት በአዎንታዊነት በመቀበሉ ነበር። (በኋላም፥ የሲዳማ ሽማግሌዎች መለስን ቢሮው ድረስ ሂደው ሲያናግሩት ጥያቄውን ለመመለስ አለመፈለጉን ለመግለፅ ያደረገው ነገር፣ "አሁን ሰባት ሰዓት ሆኖልአ፥ ርቦኛል!" ብሎ አዳራሽ ውስጥ እንዳሉ ትቶአቸው መውጣት እንደነበረ በቦታው የነበሩ ሰው አጫውተውኛል።)

ጠቅላይ ምኒስትር መለስ፥ ይሄንን መሠረታዊ ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ ደንበኛ የማፍራት ሥራ በመስራት ጊዜውን አሳለፈ። ሃዋሳ ከተማ ውስጥ ለአንዳንድ የሲዳማ ልሂቃን መሬት በመስጠት፥ የክልሉ ፕሬዝዳንት ሲዳማ እንዲሆን በማድረግ ፥ የክልሉ ካቢኔ በአብዛኛው (በተለይ በክልሉ ምክትል የቢሮ ሃላፊነት ደረጃ) የሲዳማ ልሂቃን እንዲሆኑ በማድረግ፥ የከተማው ሥም 'አዋሳ' ከመባል ይልቅ 'ሃዋሳ' በሚለው ትክክለኛ ስሙ እንዲጠራ በመቀበል ፥ ወዘተ የክልልነት ጥያቄውን ለማድበስበስ ሞከረ።

አልሰራም። አሁንም፥ ወደፊትም እንዲህ ዓይነቱ ደንበኛ-ደጋፊ (co-opted client) የማፍራት ፖለቲካዊ ሸፍጥ የሚሰራ አይመስለኝም።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሃዋሳ የበጎ ፍቃድ ጉብኝት ባደረገበት ወቅትም ሕዝቡ ይሄን ጥያቄ በአፅንኦት፥ በግልፅ አንስቶአል። ይሄንንም በጨዋነትና ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ አድርጎአል።

ሰሞኑንም በፍቼ-ጨምበላላ በዓል ዋዜማና በእለቱ በሰላማዊ መንገድ ገልፆአል። ሕገ-መንግሥታዊ መብቱን ለማስከበር በትዕግስት ለሁለት አስርት ዓመታት ታግሷል፥ ጠብቋል። አሁንም በትዕግስት እየጠየቀ፥ እየጠበቀ ይገኛል።

ትናንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሄሃን ጥያቄ ከሌሎች የድንበር ጥያቄዎች ጋር በማመሳሰል ለማወሳሰብ መሞከሩ አሳዛኝ ከመሆን አልፎ መሰሪነት ነው።

የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ሌላ፥ ክልል የመሆን ጥያቄ ሌላ። የድንበር ይገባኛል ጥያቄ መከራከሪያ ጭብጥ የሚሆነው ክልል የመሆን ጥያቄ ከተመለሰ በኋላ ነው። የራሱ ክልል ለሌለው ሕዝብ የምን/የቱን ወሰን ነው የምታስከብርለት?

የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄ ቀላል ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ ነው የጠየቀው። "ክልል የመሆን መብታችንን ለመጎናፀፍ በሕጉ መሠረት ሬፈሬንደም ይፈቀድልን፥" ነው ያለው። የማንንም ድንበር ይገባልኛ አላለም። (የዳሌ ወረዳን ማካለል ጉዳይ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ተሰጥቶበትም እስከዛሬ ሳይተገበር እንደቀረ ይታወልቃ። ሌላ የድንበር ጉዳይ የለም። ካለም ከክልልነት በኋላ የሚታይና በሕግ አግባብ የሚመለስ ይሆናል።)

የድንበር/ወሰን ጉዳይ ሕገ-መንግሥታዊ መትፍሄ አለው። አንቀጽ 46 እና 47 በግልፅ ያስቀምጡታል። እስካሁንም ያለው ችግር ኢሕአዴግ ሕገ-መንግሥቱን አለማክበሩ ነበር፥ አሁንም ነው። አከላለሉን በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ቢያደርጉት ኖሮ ደቡብ የሚባል ክልል ባልኖረም ነበር። ይሄ ነው በዘፈቀደ አሰራር፤ ይሄ ነው የማን-አለብኝነት ተግባር ማለት።

በሕገ-መንግሥታዊ አከላለሉ ዙሪያ አለመግባብት ካለ ችግሩን ለመፍታት በሕግ ረገድ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አለ፤ በአስተዳደር ረገድ ደግሞ የፌደራልና አርብቶ-አደሮች ጉዳይ ሚኒስቴር አለ። እነዚህ ተቋማትም በ Intergovernmental Relations መርሕ፥ ሕግና ተቋማት ይታገዛሉ።

ድንበር/ወሰን በፌደሬሽን ውስጥ ቋሚ ላይሆን ይችላል። በየጊዜው እየታየ (እንደሕዝቡ እንቅስቃሴ ሁኔታ፥ እንደዴሞግራፊው ለውጥ ሂደት፥ እንደመሠረተ-ልማት አውታሮች መዘርጋትና አስተዳደራዊ አመቺነት ሁኔታ መቀያየር፥ እንደ አካባቢያዊ ጥቅሞች ሁኔታ መለዋወጥ፥ ወዘተ) መፈተሽ እንደሚገባው የታወቀ ነው።

ለዚህ የሚጠቅም ፖለቲካዊ ተቀባይነት ያለው፥ አካታች፥ አገራዊ የባለሙያዎች ኮሚሽን (በየአስር ወይም ሃያ ዓመቱ የሚታደስ) መፍጠር ይገባ ነበር፥ አሁንም ይገባል። ይሄ መደረግ አለበት።

በእውቀት ላይ የተመረኮዘ፥ ሰላምን የሚገነባ፥ ለሁሉም በሚጠቅም መንገድ የወሰን ጉዳይን እያጠና የመፍትሄ አቅጣጫ የሚጠቁም፥ ተቋም መፍጠር አስፈላጊ ቢሆንም የመብት ጥያቄዎችን ለማፈን ምክንያት አይሆንም።

ጠቅላይ ምኒስትሩ ትናንት እንዳለው የድንበር ኮሚሽን ተቋቁሞ፥ ሁሉንም የድንበር ግጭቶች አጥንቶ፥ አከላለሉን ፈትሾ፥ እስኪከልሰው (revise እስኪያደርገው) ድረስ የናንተን የክልልነት መብት መመለስ አይገባም ማለት፣ በቅንነት የተባለ ከሆነ፣ ይሄ ሕገ-መንግቱን፥ ሕዝቡን እና አገሩን፥ እንዲሁም ሥርዓቱን አለማቅወ ነው።

ከ20 ዓመት በላይ በብዙ መከራ የታገሰን ሕዝብ "ክልልነትን እራሱን ላስቀርልህ ስለሆነ ታገስ" ማለት፣ ንቀት ነው። ከመለስ ዜናዊ "እርቦኛል" ምክንያት ምንም አይለይም።

ይሄንን ለፖለቲካ ትርፍ ብቻ ብሎ ('ክልላዊ ወሰን የዜጎችን የመንቀሳቅስ ነፃነት ይገድባል' የምትለውን የዛኛው ቤት ልጆች ነጠላ ዜማ ለማዜም) ከሆነ የችግሩ ክብደት ገና አልገባውም ማለት ነው።

ከዚህ ሁሉ በተለየ ሁኔታ ለሕዝቦች መብት ክብር ሳይሰጡ፥ ለሕግና መንግሥታዊ ተቋማት ሥራና ሕገ-መንግሥታዊ አሰራር ተገቢውን ቦታ ሳይሰጡ፥ በአፈ-ጮሌነትና ባልበሰሉ የስብከት ቃላት ብቻ፥ ሕዝቦች እየሞቱለት ያለን የመብት ጥያቄ ለማለፍ መሞከር እብደት ነው።

መብትን በአግባቡ አለመመለስ የሕወኃት ግጭት ቸርቻሪዎችን ካፒታል ማሳደግ ነው። እነርሱ፥ ብሶቱን እያጋነኑ በመስበክ፥ ሕዝቡ በሕግ፥ በተቋማት፥ እና በሥርዓት መተማመን እንዳይኖረው፥ ተስፋ እንዲቆርጥ፥ ብሎም ወደ ኃይል ተግባር በመግባት ከሌሎች ጋር እንዲጋጭ እንዲነካኩት ዕድል ይሰጣል።

ግጭት ማስቀረት ከፈለግህ መፍትሄው ይሄን ያህልም ከባድ አይደለም፤ መፍትሄው ቀላል ነው፦የሕዝቡን መብት አክብርለት። ጥያቄውን በግሕ አግባብና ተቋማዊ በሆነ መንገድ መልስለት።

ብሩክ ሰንበት!!!