Gudumaale

   Sidaamu Daga Budu Battala
Connecting Sidama People

የሲዳማ ህዝብ ክልል የመሆን ጥያቄና ቀሪው የህዝበ ዉሳኔ (ሪፈረንዴም)ጉዳይ፣ ምንነቱ፣ ኣፈጻጸሙና የደቡብ ክልል ምክር ቤት ህገመንግስታዊ ግዴታ

በኪንክኖ ኪኣ

ቀደም ሲል የሲዳማ ህዝብ ክልል ጥያቄ እንደምታ ከሌሎች ፌዴራል ሥረዓት ከሚከተሉ ሀገሮች ጋር በንጽጽር ለማቅረብ ሞክሬ ነበር። በጽሁፉ ማጠቃለያም ክልል የመሆን ጥያቄ በሌሎች ፌዴሬሽኖችም የተለመደና መንግሥታት በጊዜው ሂደት ውስጣዊ መልካችዉና ቅርፃቸው መቀየሩ አይቀሬ መሆኑንና የሲዳማ ህዝብ ጥያቄም የኢትዮጵያን አንድነትም ሆነ የፌዴራል ሥርዓቱ ፈተና አድርጎ መውሰድ የተሳሳተ ምልከታ መሆኑን ጠቅሻለሁ። በመጨረሻም የሲዳማ ህዝብ ክልላዊ መንግሥት እዉን ለመሆን በመቃረቡ ከድቡብ ክልል ጋር ሊፈፀም ያለው ፍቺ በምን መልኩ እምደሚከናወን ለማሳየት አሁን ስለቀረው ህዝበ ዉሳኔ (ሪፈሬንደም) አንዳንድ ነጥቦችን እንደሚከተለው አቅርቤያለሁ።
================================================

ህዝበ ዉሳኔ የሚለዉ ሀሳብ በተለያየ መንገድ ይገለጻል። በሰፊው ተቀባይነት ያገኘዉን ትርጉም የሚሰጠዉ Yves Beigbeder በOxfor Public International Law Series (2011) ላይ ሲሆን ”A Referendum is a direct vote in which an entire electorate is asked to answer a question on a particular proposal“ በማለት ይተሮጉማል። በኣጭሩ ህዝበ ዉሳኔ ማለት መራጩ ወይም ድምጽ ሰጪው ህዝብ በኣንድ የፖለቲክስ ዉሳኔ በሚፈልግ ጉዳይ ላይ በቀጥታ ድምጽ የሚሰጥበት ሂደት ነው።

Cambridge Dictionary በበኩሉ “A Referendum is a vote in which all the people in a country or an area are asked to give their opinion about or decide an important political or social question.” ይላል። በኣጭሩ ሲተሮጎምም ህዝበ ዉሳኔ ማለት የሃግሪቱ ህዝብ በሙሉ ወይም የሚመለከተው የሀገሪቱ ክፍል በኣንድ ፖለቲካዊ ወይም ማህበራዊ ጥያቄ ወይም ጉዳይ ላይ በቀጥታ ድምጽ የሚሰጥበትን ሂደት ያመለክታል። ከዚህም ለማየት የሚቻለው ሪፈረንደም የኣገሪቱ ህዝብ በሙሉ የሚሳተፍበት ወይም ውሳኔው የተወሰነውን የኣገሪቱን ክፍል ብቻ የሚመለከት በሆነ ጊዜ የሚመለከተው ህዝብ ብቻ የሚሳተፍበት መሆኑን ነው። ከዚህም በላይ፣ ኣንዳንድ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የመንግሥት ሹማምንት በደመነፍስ ወይም በፖለቲካ ፈላጎት ተነሳስተዉ የፖለቲካ ዉሳኔ ብያስተላልፉ የተፈለገውን የህዝብ ተሳትፎና ፍላጎት ለማረጋገጥ ስለማይቻል ህዝቡ በራሱ እንዲውስን ይደረጋል።

ሪፈረንደም ብዙውን ጊዜ የሚዘወተር ተግባር እንዳልሆነ የህግና ፖለቲካ ምሁራን ይናገራሉ። ምክኛቱ ደግሞ በኢኮኖሚ ረገድ ከፍተኛ በጀትን የሚፈልግ በመሆኑና፣ በሌላ በኩልም ሪፈረንደም በወሳኝ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ ውሳኔ ለመስጠት ሀገራቱ ይጠቀሙበታል።

በዚህ ረገድ ሪፈረንደም ብዙውን ጊዜ ተገባራዊ የሚደረገው የኣንድን ህዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብትን ለማረጋገጥ እንደሆነ ከላይ የጠቀስነው የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ጽሁፍ ያስገነዝባል። ሪፈረንደም ለማደራጀት ብዙ ዝግጅቶች የሚያስፈልጉ ሲሆን በኣንዳንድ ኣገሮች ሪፈረንደም እንዲደራጅ ሥልጣን የሚሰጥ ህግ ጭምር እንዲወጣ ሊደረግ ይችላል።
=================================================

የሪፈሬንደም ዓይነቶች
=============================
ሪፈሬንደምን በተሻለ ምልኩ ለመረዳት ጸሓፊዎች የሚጠቀሙበት ዋነኛ መለኪያ ሪፈሬንደሙ ያለውን ሥልጣንና የሚኖረዉን ውጤት በማየት ነው። በዚህም መሠረት ሁለት ኣይነት ሪፈሬንደም እንዳለ ለማየት ይቻላል። የሄውም 1ኛ ኣስገዳጅ ህዝበ ዉሳኔ እና 2ኛ ኣስገዳጅ ያለሆን ውይም በኣማራጭ የሚካሄድ ህዝበ ዉሳኔ በመባል የሚታወቁ ናቸዉ።

ኣስገዳጅ ህዝበ ዉሳኔ እንደስሙ የኣስገዳጅነት ሥልጣን ያለው ነው። ይህም በሁለት መልክ ይገለጻል፣ ኣንደኛው ሪፈሬንደሙን ማካሄድ በራሱ ብህጉ ወይም በህገምንግሥቱ ውስጥ የተደነገገ በመሆኑ የግድ መካሄድ ያለበት ነው። ሁለተኛዉ፣የህዝበ ውሳኔው ውጤት ለነገ ሳይባል መተግበር የሚገባው መሆኑን ማየት ያሻል። በዚህም መሠረት ኣስገዳጅ የሆነውን ሪፈሬንደም ለመተግበር የህዝብ ተወካዮችም ይሁኑ የመንግስት ሥራ ኣስፈጻሚው ኣካል ሊሽረዉ የማይችለው ሲሆን በውጤቱም ሊገዛበት የገደዳል ማለት ነው። ይህም በዋናነት በኣገር ደረጃ ኣዲስ ህገመንግስት ለማጽደቅ ወይም በኣገራት መካከል የሚፈጠረውን የድንበር ግጭት ለመፍታት እንዲሁም የኣንድን ህዝብ የራስን ዕድል በራስ ለማስተዳደር ሲፈልጉ ሥራ ላይ የሚውል እንደሆነ ለመገንዘብ ይቻላል።
ሁለተኛው የሪፈሬንደም ዓይነት ኣስገዳጅ ያልሆነ ሲሆን እንደሁኔታው ኣስገዳጅ ሊሆንሚችል ሆኖ በዋናነት ሴንስቲቭ በሆኑ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በመንግስት ፍላጎት የሚፈጸም ነው። ውጤቱ የግድ መተግበር ኣለበት የሚባል ባይሆንም መንግሥት ግን የዚህን ዉሳኔን ውጤት ቸል ሊለው እንደማይገባ ይቬዝ ቤይግበዴር የተባሉ የዓለም ኣቀፍ ህግ ምሁር ከፍ ሲል በተጠቀሰው ጽሁፋቸው ላይ ይመክራሉ።

የሪፈሬንደም ዓላማ፣
=========================
ከፍ ሲል እንዳየነው ሪፈሬንደም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሊተገበር የሚችል ነው። በዋናነትም ኣዲስ ህገመንግሥትን ለማጽደቅ፣ ነባር ህገመንግሥትን ለማሻሻል፣ የዓለም ኣቀፍ ስምምነቶችን ለማጽደቅ፣ የኣንድ ህዝብ ነጻነት መታወጁን ለማረጋገጥ፣ በኣንዲት ሀገር ውስጥ ክልላዊ መንግሥት የማደራጀት ፍላጎት፣ እንዲሁም በሌሎች ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ሞራላዊ ጉዳዮች ላይ ዉሳኔ ለመስጠት ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነ ምሁራን ይስማሙበታል። 
ህዝበ ዉሳኔ ብዋናነት የኣንድ ህዝብ ውይም ብሄር የራሱን ዕድል በራሱ ከመወሰንና የክልል ምሥረታ ጥያቄ ጋር ተያይዞ በሰፊው የሚሠራበት መሳሪያ እንደሆነ ሊሠመርበት ይገባል።
========================================

በህዝበ ዉሳኔው ላይ እነማን ይሳተፋ?
===============================
ከላይ ባጭሩ እንዳነሳነው ህዝበ ዉሳኔ የሚካሄድባቸው ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጣቸው በመሆናችዉ በርካታ ኣካላት ወይም ተቍማት ይሳተፉበታል። ከነዚህም መካከል፣ መራጮች ወይም ደመጽ ሰጪዎች፣ ቅስቀሳ የሚያደርጉ ኣካላት፣ የምርጫ ቦርድ ወይም ኮምሽን፣ የድምጽ ቆጠራ ኃላፊዎችና ኦፊሴሮች፣ ሚዲያ ወዝተ ናቸው። 
===============================================

ህዝበ ዉሳኔ (ሪፈሬንደም) በኢትዮጵያ ህግ በአጭሩ፣
=====================================
በኢፌድሪ ህገመንግሥት ዉስጥ ህዝበ ዉሳኔ ማደራጀት አስፈላጊ ከሚሆንባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ጉዳይ ተጠቅሶኣል። ይሄውም በኣንቀጽ ፬፯ ሥር የተመለከተ ሲሆን ጉዳዩም ከብሄሮች ወይም ህዝቦች የራሳችው ክልል ለመመሥረት በሚፈልጉበት ጊዜ የሚተገበር እንደሆነ ይታያል። በህገመንግሥቱ መሠረት ማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ወይም ህዝብ የራሱን ክልል ልመመሥረት ሲፈልግ ጥያቄው በራሱ ምክር ቤት ብሁለት ሦስተኛ ደምጽ መጽደቅ የሚገባዉ ሲሆን ቀጥሎም ለክልል ምክር ቤት ይቀርባል። የክልል ምክር ቤት ድርሻም በህገመንግሥቱ ላይ ተጠቅሶኣል። በአንቀጽ 47 (3ለ) ላይ የክልሉ ምክር ቤት ሚናም ሪፈሬንደም ማደራጀት እንደሆነም ለማየት ይቻላል።

ከፍ ሲል እንደቀረበው ሪፈሬንደም እንዲካሄድ ከሚገፋፉ ምክንያቶች መካከል የኣንድ ህዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰንና የራሱን ክልል መንግሥት ለማቍቍም ጉዳይ ዋነኛ መሆኑን ኣይተናል። ይህ አሠራር በሌላውም ዓለምም ተቀባይነት ያገኘ እንደሆነም ይታያል። በመሆኑም የክልል ምክር ቤት ሌላ ሚና የለውም፣ ብቸኛው ሚና ሪፈሬንደም ማደራጀትና ጥያቄውም በኣብላጫ ድምጽ ድጋፍ ሲያገኝ የቀደመው ክልል ምክር ቤት ሥልጣኑን አዲስ ለሚቍቍመው ክልል የማስረከብ ህገምንግሥታዊ ግዴታ እንደተጣለበት በገለጽ ተቀምጦኣል። ይህም መሆን የሚገባው በኣንድ ዓመት ጊዜ ውሰጥ ነው።

በህገመንግሥቱ መሠረት ህዝበ ዉሳኔ ማደራጀት ኣስገዳጅ ነው ወይስ አይደለም?
===============================================

ከፍ ሲል በመግቢያችን ላይ አስገዳጅና አስገዳጅ ያልሆነ ሪፈሬንደም ምንነት አይተናል። በዚህም መሠረት ህዝበ ውሳኔውን አስገዳጅ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ዋነኛው ህዝበ ዉሳኔ ማካሄድ በህገመንግሥቱ የተደነገገ ሲሆንና አይቀሬ በሆነ ጊዜ ነው። የራስን የክልል መንግሥት ማደራጀት ከፍተኛ የፖለቲካ ፍላጎትና ሥሜት የሚታይበት በመሆኑና ህዝቦችም ይህንን መብታቸውን አንደዋስትና ስለሚቆጥሩት ህዝበ ዉሳኔው በአግባቡ እልባት ሊሰጠው የሚገባ ሀገመንግሥታዊ ግዴታ ጭምር እንደሆነ ከድንጋጌው ይዘትና መንፈስ ለመገንዘብ ይቻላል። 
የጉዳዩን አስገዳጅነት ክሚያሳዩ ሌሎች ምክኛቶች መካከል ህዝበ ዉሳኔው በምን ያህል ጊዜ ውስጥ መካሄድ እንዳለበት ጭምር በህገመንግሥቱ ተቆርጦ በመቀመጡ የህዘበ ዉሳኔውን መካሄድ አይቀሬ ያድርገዋል። በህገመንግሥቱ መሠረት ትልቁ የሥልጣን ምሰሶና ባለቤት የሆኑት ብሔሮችና ብሔረሰቦች ወይም ህዝቦች በመሆናችው (አንቀጽ ፰) የራሳችውና የሚመጥናቸውን የመንግሥት መዋቅር በፈለጉትና በፈቀዱት ደረጃ የመመስረት ሙሉ መብት ያላቸው በመሆናቸው ጭምር ነው። በመሆኑም፣ ሪፈሬንደም ማካሄድ በህገመንግሥቱ በአማራጭነት ሳይሆን በግዴታ መልክ የተደነገገ ሰለሆነና ማናቸውም የመንግሥት አካላት ሀገመንግሥቱን የማክበርና የማስከበር ግዴታ የተጣለባቸው በመሆኑ (አንቀጽ ፱፣ ፩፫) ከዚህ ውጪ ለጉዳዩ እልባት ለመስጠት መሞከር አደገኛ እና ኢ=ህገመንግሥታዊ የሆናል። ሂደቱማ ሆነ ዉጤቱ በህገመንግሥቱ መሠረት ዉጤት አይኖረውም።
===============================================

ሪፈሬንደም የመፈጸም ኃላፊነት ማንን የመለከታል?
=====================================
እንግድህ ከላይ እንደቀረበው፣ የክልል ጥያቄ በቀረበ ጊዜ የክልል ምክር ቤት ህዝበ ዉሳኔ ያደራጃል የሚለዉን ከመደንገግ ባለፈ የቀረውን ጉዳይ ማን መፈፀም እንዳለበት የሚግልጽ ድንጋጌ ኣላስቀመጠም። ይህ በሆነበት ሁኔታ ጉዳዩ ማንን እንደሚመለከት ማፈላለጉ ተገቢ ነው። መቼስ የጉዳያችን ማጠንጠኛ የሆነዉ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ሪፈረንድም አካሂዶ ፣ ድምጽ ሰቺዎችን መዝግቦና ድምጽ ቆጥሮ ያስረክባል ለማለት ይከብዳል። ምክኛቶቹ ደግሞ የምክር ቤቶች ኃላፊነትና ተግባር የተለየ ነው። በተጨማሪም የክልል ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ፍላጎትና ጥቅም ስላለውና ፊቺውንም አይፈልግም ተብሎ ስለሚገመት እየተፋታው ያልውን ህዝብ ጉዳይ በቅንነትና በገለልትኝነት ያስፈጽማል ተብሎ አይጠበቅም። ገለልትኛ የሆናል ቢባል እንኳን የምክር ቤቱ አባላት በመርጫዉና በቆጠራው የሚሆን ቴክንካዊ እውቀት ይሌላቸው ፖለቲከኞች በመሆናቸውና ተግባራቸውም ሌላ ስለሆነ አይመለከታቸውም።

ስለሆነም ሂደቱን የሚፈጽም ተገቢውን አካል መፈለግ ተገቢ ንው። ማንኛውም ህገመንግሥት በባህሪው ጠቅላላ ይዘት ስላለው ለሁሉም ጉዳዮች ምላሽ ስለማይሰጥ ሌሎች ህጎችን መፈተሽ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ደግሞ የሚናገኘው የኢትዮጵያ ምርጫ ህግ እና የብሄራው ምርጫ ቦርድ ነው። ነጻና ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ እንደሚደነግ ግ የኢፌድሪ ህገመንግሥት አንቀጽ ፲፪ ላይ ተመልክተዋል። አሁን ለያዝነው ጉዳይ አግባቢነት ያለው አዋጅም የተሻሻለዉ የምርጫ ህግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 ዓም ነው። በአዋጁ መግቢያ ላይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በየደረጃዉ በሚካሄዱ ሁሉአቀፍ ጉዳዮች ላይ በእኩልነት ላይ በተመሠረተና በምሰጢር ደምጽ አሰጣጥ ፈቃዱን በነጻነት የሚገልጽበት ነጻ፣ ሠላማዊና ፍጥሓዊ ምርጫ በገለልተኝነት የሚፈጽም ተቍም ማቍቍም አስፈላጊ በመሆኑ የምርጫ ህግ መውጣቱን ይናገራል፣ ስለሪፈሬንደምም ያወሳል።

ሪፈሬንድም በኣዋጁ አንቀጽ 2(9) ላይ ህዝበ ዉሳኔ ማለት "በኢፌድሪ ህገመንግሥት መሠረት ሲወሰን ይህዝብ ፍላጎትን ለመለካት እና የህዝብን ዉሳኔ ለማወቅ ደምጽ የሚሰጥበት ሥርዓት ነው።" እንግድህ በህገመንግሥቱ መሠረት ሲወሰን የተባለው ሐረግ በኣንቀጽ 47 ሥር የተደነገገውን ለማመላከት ነው።
በሌላ በኩል በሪፈሬንደሙ ላይ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥልጣን እንዳለው የሚደነግገው አንቀጽ 3 ሲሆን በዚህም መሠረት የመርጫ ህጉ ለጠቅላላ ምርጫ፣ እንዲሁም እንደ አግባቢነቱ በህገመንገሥቱ መሰረት ለሚካሄድ ህዝበ ዉሳኔ ተፈጻሚ የሆናል በማለት ይደነግጋል።

በኣዋጁ አንቀጽ 7 ላይ የምርጫ ቦርዱ ሥልጣንና ኃላፊነት የተመለከተ ሲሆን #ቦርዱ በህገመንግስቱ እና በዚህ አዋጅ መሠረት የሚካሄድ ማንኛውንም ምርጫ እና ህዝበ ውሳኔ በገለልተኝነት የማስፈጸም ኃላፊነት እንዳለበት በኣንቀጽ 7(1) ስር ተመልክተዋል።
=================================================
ማጠቃለያ፣ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ሪፈሬንደም በኣስቸኳይ ለማደራጀት ያለበት ግዴታ
=================================================

ከዚህ ቀደም በሌላ ጽሁፍ የሌሎች ፌዴራል ሥርዓት የሚከተሉ ሀገሮችን ትመክሮ ተመልክተናል። ከነዚህም አገሮች መካከል አውስትራሊያ ተጠቃሽ ስትሆን የሀገሪት ህገመንግሥት በኣንቀጽ 121 እና 124 ላይ ኣዲስ ክልል መፍጠር ስለሚቻልበት ሁኔታ ይደነግጋል። በዚህም መሠረት አዲስ ክልል ሲመሠረት የኣገሪቱ ፓርላማ እና ፊቺ የተጠየቀበት ክልል ምክር ቤት የግድ ፈቃድና ይሁንታ ማግኘት ይኖርበታል። ሪፈሬንድምንም በተለያየ ጊዜ ኣካሂደዋል።

የኢትዮጵያ ህገመንግሥት ግን ከዚህ የተለየ አካሄድን የሚከተል ሲሆን የክልልም ሆነ የክልል ምክር ቤቶችን ድጋፍና ሥምምነት የሚጠይቅ ድንጋጌ አላካተተም። ስለሆነም በህገመንግሥቱ የፌዴራሉ ፓርላማ በክልል ምሥረታ ሂደት ላይ ያለው ሚናም ያልተገለፀ ሲሆን አለመገለጹም ሚና እንዳይኖረዉ እንደተፈለገ ያሳያል።
የደቡብ ክልል ምክር ቤት በበኩሉ ጉዳዩን ለመፈጸም ካለበት ግዴታ አንፃር ህዝበ ዉሳኔ ለማደራጀት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ለህገመንግሥቱና ለህገመንግሥታዊ ሥርዓቱ ያለዉ ታማኝነት የሚለካበት መለኪያ ነዉ።

በመሆኑም አስፋልጊውን ዝግጅት ማድረግና በጀት መመደብ፣ እንዲሁም ከብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጋር መነጋገር አለበት። ቀደም ሲል ኢህአዴግ ምክረ ቤት ጥያቄውን መቀበሉ በፖለቲካዉ ረገድ ያለበትን ጫና ቀንሶለታል። 
ከዚህ ባለፈ ግን የሥልጣን ለኩን ማወቅም አለበት። ምክር ቤቱ በሲዳማ ክልል ጥያቄ ላይ የወያየትም ሆነ ድምጽ የመስጠትም የሁንታና ድጋፍ የመስጠትም ሆነ የመቃወምና ሪፈሬንደሙን ጊዜ የማራዘም ሥልጣን በህገመንግሥቱ ኣልተሰጠውም፣ ስለሆነም በነዚህ ጉዳዮች ላይ እጁን ከመሰብሰብ ውጪ መስደድ አይችልም። ይህም ማለት በጉዳዩ ላይ የመወሰን ሙሉ መብት ያለው የጠየቀው ህዝብ=የሲዳማ ህዝብ ብቻ ንው።

ይክልል ምክር ቤት ዉሳኔ ማስተላለፍ ባይችልም ሪፈሬንደሙን በተባለው አንድ ዓመት ዉስጥ ለማደራጀት አስፈላጊዉን ሁሉ ማድረግ በህገመንግሥቱ የተጣለበት ግዴታው ነው። ከላይ እንደጠቀስኩት አስቀድሞ ለዚህ ተግባር የሚያስፈልግ በጀትና የሰው ኃይል ማዘጋጀት አለበት፣ ከምርጫ ቦርድ ጋር በመነጋገር በጋራ መፈፀም በሚችሉበት ሁኔታ ላይ የጋራ መግባባት መፍጠርና ከሲዳማ አስተዳደ ጋርም በመናበብ በቅርበት መሥራት የጠበቅበታል።

ሌላው ምን ጊዜም የማይታለፈውና በጥንቃቄ መፈፀም ያለበት ጉዳይ ሪፈሬንደም ለማደራጀት በህገመንግሥቱ የጊዜ ገደብ በኣግባቡ የመከተል ገዴታ ነው። ህገመንግሥቱ በ፩ ዓመት ጊዜ ውስጥ ህዝበ ዉሳኔ ይደራጅ ሲል፣ የግድ ፩ ዓመት እስከሚያልቅ ቁጭ ተብሎ የጠበቅ ማለት አይደለም። የመጨረሻው ጣሪያ ለማመላከት ብቻ የተቀመጠ ነው። አንድ ዓመት ጊዜም በጣም ኣጭር ሲሆን ምን ያህል የሀዝብ ክልል የመሆን ጥያቄና ዉሳኔ በኣጭር ጊዜ ውስጥ በኣግባቡ ምላሽ እንዲያገኝ በህገመንግሥቱ ትኩረት እንደተሰጠው ያሳያል። በተጨማሪ ሥራ አስፈፃሚው ጥያቄውን መነሻ አድርጎ የተለያዩ የትንኮሳ ተግባሮችን በመፈፀም ህዝቡን እንዳያጉላላና ሥላጣኑን በኣግባቡ እንዲጠቀም የተበጀ ለጓም ጭምር እንደሆነ በግልጽ መታወቅ የኖርበታል።
================================================

በኣጠቃላይ በሪፈሬንደሙ የሲዳማ ተዎላጅ የሆነና (ድምጽ ለመስጠት ዕድሜ የደረሰ) ይሳተፋል። ከዚህ ሥራ አስቀድሞ የቅስቀሳና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራዎች ተጠናክረው መሠራት እንደሚገባቸው የሌሎች አገሮች ተሞክሮ ያሳያል።
በህገመንግሥቱ መሠረት ሪፈሬንደም ማደራጀት አስገዳጅ እንጂ አማራች ለመሆኑ፣ የተሰጠውንም የጊዜ ገደብ መጠበቅ የግድ ነው። ሪፈሬንደም ሳይደራጅ በስዉር ፖለቲካዊ መንገድ ጉዳዩን ለመፍታት መንቀሳቀስም ኢህገመንግሣታዊ አካሄድ ሲሆን ዉጤቱም ዋጋ እንዳይኖረው ያድርጋል። በመሆኑም የክልሉ ምክር ቤትም ሆነ ደኢህዴን (ሬዳና) ህገመንግሥቱና ህገመንግሥታዊ አካሄድን መከተልና መተግብር አለበት። ይህ ሳይሆን ሲቀር ሊከሰት የሚችለው አደጋ ከሚገመትው በላይ ነው። አንድ ህዝብ በራሱ ፍላጎትና ፈቃድ ክልል መሆን ከፈለገ መፍቀድና መተግበር ህገመንግሥታዊ ዋስትና ያለው አካሄድ ነው።

የሲዳማ ህዝብ ለበርካታ ዘመናት ስታገል የኖረውንና ውድ ሴትና ወንድ ልጆቹን የገበረለት ጥያቄ፣ ብቻዉን ዋጋ እምደከፍለና እምደታገለ በራሱ ድምጽ ብቻ ክልል ምሥረታውን በቅረቡ እውን ያደርጋል። ጠንካራ ሲዳማ ክልል መፈጠርና መኖር ለጠንካራ ኢትዮጵያ እውን እውን መሆን ወሳኝ ነው እንላለን።

በመጨረሻም የደቡብ ክልል ምክር ቤት በኣስቸኳይ ህዝበ ዉሳኔ እምዲያደራጅ ይህ ፀሐፊ እየጠየቀ የሲዳማ ህዝብም ጥያቄው ህገመንግሥቱ ባስቀመጠው አሠራር ዝንፍ ሳይል እንድፈፀም በኣጽንኦት በመከታ ተል ጠያቄው ምላሽ እ ንዲያገኝ ሠላማዊ ትግሉን አጥናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀርባል።

ህዝብ ያሸንፋል!!