Gudumaale

   Sidaamu Daga Budu Battala
Connecting Sidama People

የሲዳማ ህዝብ ክልልነት የሚቃወሙ ኃይሎች ዓላማ የደቡብ ክልል ዕጣ ፈንታ አሳስቧቸው ሳይሆን የእኩልነት ጥያቄ ያለመቀበል ጉዳይ ሆኖባቸው ነው። ሌሎቹ የእነዚሁ ኃይሎች ተላላኪዎች ናቸው።

by Kinkino Kia

በሲዳማ ክልልነት ጥያቄ ሰበብ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቅኝትን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። ደቡብ በወረራና በጦርነት በወቅቱ ወደ አብሲንያ ግዛት የተጠቃለለ ነው በ19ኛው መቶ ክፍለዘመን። በወቅቱ ጦርነቱን አስመልክተው የተናገሩት ንጉስ ምንሊክ፣ “ሌሎች አውሮፓውያን መላ አፍሪካንና የአፍሪካ ቀንድን ሲቆጣጠሩ እኔ ዳር ቆሜ የማይ ተራ ተመልካች አይደለሁም ብለው እንደነበር በታሪክ መዛግብት ውስጥ ተጽፎ ይገኛል (Markakis, 2011)።

ከወረራውና በኃይል ከማጠቃለሉ ክስትተ አንስቶ በደቡባዊው ህዝብና የሥልጣን core (ሰሜናዊው) ግንኙነት የቅኝ ገዥና ተገዥ ሆኖ ቆይቷል። በሂደት በ20ኛው ክፍለዘመን አጋማሽ የተቀጣጠለው የregionalism ስሜትና ያስከተለው ትግል፤ በሂደት ማዕከላዊነት መሠረት አድርጎ ሌሎች ፖለቲካል peripheries የሆኑትን ህዝቦች በመግፋት ላይ የተመሠረተውን የፖለቲካ ቅኝት አንግጫግጮ፣ በሂደትም አሸናፊ ሆኖ ወጥቷል።

ከደርግ መገርሰስ ጋር አሸናፊው ህወሃት ይሁን እንጂ አብዛኛው ጭቁኑ ህዝብ የየድርሻውን በወታደራዊ ትግል የታገዘ የእኩልነት ትግል አካሂደዋል። በኃላም ከደርግ መገርሰስ ጋር አብሮ የተደረመሰው የደርግ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን፣ የቀኝ ገዥና ተገዥ መካከል ሰፍሮ የነበረው የበላይና የበታችነት/domination and subordination/፣ በበላይነት ልግዛህ የሚለው የኢትዮጵያ ፖለቲካና old state thinking አብሮ ተንኮታኩቷል።

ይህ ያልተዋጠላቸው የቀድሞ ወረራ ተዋናዎችና ድህረወረራ ሊቃውንት በወረራውና ተከትሎ በመጣው ፊውዳላዊ ጪሰኛና ገባር ሥርዓት በህዝቦች ላይ የደረሰውን በደል በመካድና የእነሱን የበላይነትና የሃገር አቅኝነት ባለውለታነትን ትርክት በማጉላት የህዝቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጠቅለል ተደርጎ ሲታይም የእኩልነትን ጥያቄ ሲያጥላሉና ሲያወግዙ ከርመዋል። ይህ ውግዘት በ አሁኑ ወቅት ከፍተኛውን የዘመቻ መልክ ይዞ ተጠናክሯል።

የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ ለምን በዚህ ደረጃ የጥላቻና የማንቋሽሸ ዘመቻ ሰለባ እንደሆነ ለማወቅ የዚህን የፖአቲካል፡ታሪካዊ ዳራውን ማየት ያስፈልጋል። በቅኝ ግዛት ገዝተህ፣ ለፊውዳላዊቷ አገር አስተዳዳሪዎች የሚቀልብና የሚገዛ ማህበረሰብ ተደርጎ የበታችነት ማዕረግ እንዲኖረው (ሁለተኛ ዜጋ) ሆኖ እንዲኖር የተዘየዴ ህዝብ ነው። ይህ ሲዳማን ብቻ ሳይሆን እንደሲዳማ ህዝብ የተጨቆኑ ህዝቦችን በሙሉ የሚመለከት ነው። ይህ ህዝብ የራሴ ክልላዊ መንግሥት ይኑረኝ ማለቱ ሥጋትንና ጥላቻን አስከትሏል። በአንድ በኩል፣ የበታች አድርገን የገዛነው ህዝብ፣ የራሱን አከባቢ ያስተዳድር መባሉ በራሱ አስከፍቶን እያለ ይባስ ብሎ መንግሥት ሊሁን ብሎ ይነሳ እንዴ?፤ ተደፈርን የሚል nostalgic mentality ቀስቅሷል።

እንግዲህ ሲዳማ ጠንካራ ክልላዊ መንግሥት ሲመሠርት የሃገሪቱን የፖለቲካ ኬክ አብሮ የሚቆርስ፣ በጋራ የሚወስን፣ ታዛዥና ተበዝባዥ ብቻ ሳይሆን የራሱን ድምጽና ድርሻ ያለው ህዝብ ወደመሆን ይሸጋገራል። የሥልጣን ሽኩቻውንም ይቀላቀልና የሥልጣን ፉክክሩን ሚዛን ሊያዛባ የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል። ከሁሉም በላይ ወደማዕከላዊ የሥልጣን ቀጠና ማስጠጋትና በእኩልነት ሚዛን አብሮ ኬክ ለመቁረስ መድረስን የማይቀበሉት ፈተና የሆነባቸው አካላት በጥላቻና በጠባብ ብሄርተኝነት በመፈረጅ በሌላው ህብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖረው፤ ካልሆነም ሌሎች ዜጎች በጥርጣሬ እንዲያዩት ለማድረግ ሰፊ ሥራ ሠርቷል። ከአንድ መንደር ተጠራርተው በመገናኘትና ለ አንድ ወገን የፖለቲካ ጥቅም በመቆም፣ በእብሪት ግን ለኢትዮጵያ የተቆረቆሩ መስለው ለራሳቸው ወገን ሲቆረቆሩ ሌላውን በጠባብ ብሄርተኝንተ ይከሳሉ።

ይህንን አላማቸውን ለማሳካት የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ። ሌሎች ዘጠኙ ክልሎች እያሉ ያልተበታተነችን አገር ትበታተናለች ይላሉ፤ የምስኪኖችን ልብ ለመብላት። ደቡብ ሲፈርስ አንድነት ይጠፋል ይላሉ፤ አንድነትን ያፍላጎትና ያለተገቢ ፖለቲካዊ መፍትሔ በጫና በማጎር ማምጣል የሚቻል ይመስል። ይባስ ብለው፣ ደቡብ በጋራ እንቨስት ያደረገው በጀት ለምን ሲዳማ ይወስዳል ይላሉ፤ የሌሌን ሃተታ ሲዘረዝሩ። ቢኖርም እንኳን ሲዳማ ከእንፓዬሩ የሚገነጠል ህዝብ አይደለም። ከኢትዮጵያዊነቱም ሊገፉት የሚዳዳቸው የዜግነት ካርድ ሰጪዎችም ሞልተዋል።

እነዚህ ማሳበቢያና ማደናገሪዎች አልፎም ማደናቀፊዎች ናቸው። ትልቁ ሚስጢራቸው፣ እኩልነትን የመቃወም ፖለቲካ ነው። በእኩል ደረጃ አንቀመጥም፣ ወደዛች ከፍታ አንቀበላችሁም፣ አይገባችሁም የሚል እሳቤ ነው። ደቡባዊ ህዝቦች ለአቅመ-ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ባለቤትነት አልደረሱም ከሚለው ትምክሂት የሚመነጭ አመለካከት ነው። ደቡብ ለነሱ ለመገዛት ብቻ የተፈጠረ እንጂ ስለራሱ እጣ ፈንታ በራሱ ሊወስን የተፈጠር አይደለም። ይህንን እኩልነትን የመገዳደር እሳቤያቸውን በተለያዩ አሳማኝ ባልሆኑ ትርክቶች እየቀባቡ የህዝብን የልማትና የመበልጸግ፣ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ፍጹም ሠላማዊና ህገመንግሥታዊ መብቱን ይጋፋሉ። ያስተጓጉላሉ።

መንግሥትም ለህዝብ ፍትሃዊ ለህዝብ ጥያቄ አግባብ ምላሽ እንዳይሰጥ ለማድረግ በማሰብ፣ ጉዳዩን አጠልሽተው ያቀርቡታል፣ ይህ ያስገኘላቸውን እድል ተጠቅመው ምላሽ መስጠት የሚገባቸውን አካላት አላስፈላጊ ምክርና ጫና ያደርጋሉ። ለዚህ ጉዳይ የሚውል ፖለቲካዊም ሆነ ፋይናንሻል ሃብት በገፍ አለ። መንግሥት ላይ ጫና ይደረጋል፤ ባንዳ ይመለመላል፤ ተጻራሪ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ወገኖችን በማፈላለግ ስፖንሰር በማድረግ ፍትሓዊ የህዝብ ጥያቄን የሚገታ አጀንዳ የበላይነት እንዲያገኝ በትጋት ይሠራሉ። አስፈላጊ ሲሆንም፣ ያልተገባ የፖለቲካ ጋብቻን ይፈጽማሉ።

አድማው፣ መገዳደሩ፣ ተጽዕኖው ሊያስቆምላቸው እንደማይችል ዘግይተውም ቢሆን ሲረዱ፣ መንግሥታዊ ሽብር /state violence/ ለመፍጠር ይንቀሳቀሳሉ። አሁጅ በዚህ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በሠላምዊ መንገድ፣ የራሱን አከባቢ ሰላምና ፀጥታ ጠብቆ፣ ህገመንግሥትዊ ሥርዓትን ተከትሎ መብቱን የሚጠይቅን ህዝብ፣ በሃሰት በመወንጀል ህገመንግሥታዊ ሥርዓትን ጥሷል በሚል ሰበብ ህዝቡን ልበቀሉት ይፈልጋሉ። ይህ ለነሱ የመጨረሻው አማራጭ ሲሆን ለሠላማዊ ህዝብ ግን የበለጠ የስኬት ደረጃ መቆናጠጥን ያሳያል። በጫናና በሃሰተኛ በፈጠራ ክሶች ህዝብን የሚበድል፤ ህገመንግሥታዊ ጥያቄዎችን ተቀብሎ በሥርዓቱ የማያስተናግድ ፣መንግሥታዊ መዋቅር ግን በህዝብ እየጠላና ተቃውሞ እየገጠመው መሄዱ አይቀርም።

የደቡብ ክልል ምክር ቤት ህገመንግሥቱ የጣለበትን ህዝበውሳኔ የማደራጀት አደራን በልቷል። የምርጫ ቦርድ የሲዳማን ክልልነት ከሚቃወሙት ኃይሎች ግንባር ቀደም ሆኖ አገልግሏል። የህዝብን ድምጽ ሳይሆን የሚቃወሙ ኃይሎችን አጀንዳ አስተጋብቷል። አገሪቱን የሚመራው መንግሥትም ጉዳዩ በተያለት ህገመንግሥታዊ በሆነ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ እርምጃ አልወሰደም። ህዝቡ ቅን በጽናት የራሱን መብት በተግባር ላይ ለማዋል በቂ ዝግጅት አድርጓል። ማነው የህገመንግሥታዊ ሥርዓትን የተጻረረውና ለመናድ የተንቀሳቀሰው? ደኢህዴን/ኢህአዴግ።

መንግሥት ይህንን ወቅት የቆዩ የህዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኙ የለውጡ አካል አድርጎ በበጎ ተቀብሎ ማስተናገድ ካልቻለና ለተከመሩ የሃገሪቱ ችግሮች ተጨማሪ የቤት ሥራ ካስቀመጠ የከፋ የፖለቲካ ችግር መፈጠሩ አይቀርም፣ የታሰበው ወታደራዊ ኃይል እርምጃም ዘላቂ መፍትሄ ይዞ አይመጣም።