Gudumaale

   Sidaamu Daga Budu Battala
Connecting Sidama People

እንደየመጨረሻ መፍትሄ የራስን ክልል በራስ የማወጅ ጉዳይና የኢፌዲሪ ህገመንግሥት አቋም፤ ከኢትዮጵያ ህገመንግሥት አርቃቂዎች እይታ አንጻር ሲቃኝ፤ 

በኪንክኖ ኪኣ

እንደመግቢያ፤

(በዚህች ጽሁፍ ላይ የህግ መከራከሪያ አይነት አገላለጽ ቢኖርበትም አንባቢዎች በጥሞና አንብበው እንዲረዱት እጠይቃለሁ)
-------------------------------------------------------------------------
የኢፌዴሪ ህገ-መንግሥት አርቃቂዎች፣ ፌዴራል ሥርዓትን የሚደነግግ ህገመንግሥትን ሲቀርፁና ይህን ያህል በርካታ ሚሊዮን ህዝብ ላላት ሀገር፣ ይህን ያህል የተለይያዩ ፍላጎቶች ላሉባት ሀገር፣ ይህን ያህል የቆዳ ስፋትና የተለያዩ ሶሺዮ-ኢኮኖንሚክ ሁኔታ ለሚስተዋልባት ሀገር 9 ክልሎችን ሲያዋቅሩ ምን ታሳቢ አድርገው ነበር? የሚለው አጠያያቂ ሆኖ የሰነበተ ጉዳይ ነው።

ከመነሻውም፣ የፌዴራል መንግሥት አወቃቀር የተቀረፀው ለዘመናት አገሪቱ ያስተናገደቻቸውን አስከፊ ጦርነቶችን ለማስቀረትና የብሄር ብሄረሰቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄን ለመመለስ እንደሆነ ይታወቃል። ኢህአዴግም በተደጋጋሚ ሲነግረን ኖሯል። በዚህም መነሻ የፌዴራል ሥርዓት ሲቀረጽ በርከት ያሉ ክልሎች ይፈጠራሉ የሚል እምነት የነበረ ቢሆንም በሽግግር ወቅት የነበሩት 14 ክልሎችም ተጨፍልቀው ወደ9 ዝቅ ብለዋል። አዲስ አበባ/Finfinee በቻርተር የሚተዳደር ሆኖ ተደራጅቷል። ሌሎች ክልሎች ተጨፍልቀው፣ በ1987 ህገመንግሥቱ ሲፀድቅ 9 ክልሎችና አዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ብቻ ተዘረዘሩ።

የአንድን ህገመንግሥት ዓላማና በአንድ ጉዳይ ላይ ያለውን አቋም ለማወቅ ከሚጠቅሙን መንገዶች መካከል ዋነኛው የአርቃቂ ኮምሽን ቃለጉባኤ/Minutes of Constitutional Assembly/drafting committee/ ላይ የሚሰፍሩ ነገሮችና በፀደቀበት ወቅት የተደረጉ ክርክሮችና የሚቀመጡ የመፍትሄ ሃሳብች ናቸው። በዚህም መሠረት የኢፌዴሪ ህገመንግሥት አርቃቂ ኮምሽን ያደረጋቸው ክርክሮችና ውይይቶች በተለያዩ ጥራዞች ታትመው ይገኛሉ።

በወቅቱ “በርከት ያለ የክልል አስተዳደር ካልፈጠርን አሁንም ክርክሩና ትግሉ አይቀርም፣ የፌዴራል ሥርዓትንና ይዞ የመጣውን መፍትሄ ቅቡልነትንም ያሳጣል…”፣ የሚሉ ክርክሮች የየህገመንግሥቱ ርቃቂዎች አምርረው ያነሱ ቢሆንም የኃይል ሚዛኑ ስላልፈቀደ አሁን ባለው አደረጃጀት ሰፍሮ ይገኛል።
የክልሎችን ስም በሚዘረዝረው አንቀጽ 47ን በተመለከተ በተደረጉ ክርክሮችም፣ አሁን ያሉት ክልሎች በህገመንግሥቱ ቢዘረዘሩም አሁን ያልተፈቀደላቸው ሌሎችም ህዝቦች ክልል መሆኑ በፈለጉ ጊዜ መፍ ሄ ማስቀመጥ ያስፈልግ ነበር።

ለዚህም እንደመፍትሄ የተቀመጠውና ከአንቀጽ 47/2 ጀምሮ የተመለከተው, በተዘረሩት ክልሎች ውስጥ የሚኖሩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች ወይም ህዝቦች የራሳቸውን ክልል መመሥረት በፈለጉ ጊዜ ማሟላት የሚጠበቅባቸውን ዝርዝር ሁኔታ አስቀምጧል። የብሄር ብሄርሰቡ ምክር ቤት በሁለት ሶስተኛ (2/3rd) ድምጽ ጥያቄውን አጽድቆ ለክልሉ ምክር ቤት እንደሚያቀርብ ደንግጓል። ውሳኔውን በጽሁፍ አድርጎ ለክልል ምክር ቤት ሲያሳውቅ፣ የክልል ምክር ቤት ሚናም በህገመንግሥቱ ሰፍሯል። ይሄውም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ህዝበ ውሳኔ እንዲያደራጅ ህገመንግሥቱ ያዛል።

የህገመንግሥቱ አርቃቂዎች የአንድ ዓመት ጊዜ ያስቀመጡት በሁለት ዋና ምክንያቶች እንደሆነ ለመመልከት ይቻላል። አንደኛው፣ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች ወይም ህዝቦች የዚሁ የፌዴራልና ህገመንግሥታዊ ሥርዓት መሥራች እንደመሆናቸውና ህገመንግሥቱም የነሱን ጥቅምና ፍላጎት ማክበርና መጠበቅ ዋነኛ ተልዕኮ በመሆኑ ይህንን ጉዳይ በትኩረት ስለሚመለከተው ነው። አገሪቱን ለጦርነትና ለማያቧራ እልቂትና ደም መፋሰስ የዳረገው የህዝቦች ጥያቄ በአግባቡ ማስተናገድ አለመቻል ስለሆነ፣ ህገመንግሥሩም ይህንን ውድቀት ትራንስፎርም/transform ለማድረግና በሀገሪቱ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለመመሥረት ቃል የገባ በመሆኑ ለህዝቦች ጥያቄ በቂ ትኩረት ይሰጣል። ይህንን በመግቢያው ላይም በማያሻማ መልኩ ደንግ ጎታል።

ሁለተኛው የአንድ ዓመት ጊዜ ተወስኖ የተቀመጠበት ምክንያት፣ ጉዳዩን የሥራ አስፈታሚው እንድወስን ከተተው፣ ሥልጣኑን አላግባብ በመጠቀምና ህዝቡን በማጉላላት ሌላ የግጭትና የጦርነት መንስዔ እንዳይሆን ልጓም ለማበጀት ታስቦ ነው፣ ለዚህም እንዲረዳ፣ ማን ህዝበውሳኔ ማደራጀት እንዳለበት ወይም ይህ የማን ግዴታ እንደሆነና በምን ያህል ጊዜ ውስጥ መፈፀም እንዳለበት በማያሻማ መልኩ ተቀምጧል።

የክልሉ ምክር ቤት በተወሰነው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ህዝበ ውሳኔ ባላደራጀ ጊዜ እንዴት ይፈፀማል?
_______________________________________________________________________________________
ሌላኛው ትኩረት የሚሻው ጉዳይ፣ የክልሉ ምክር ቤት በተወሰነው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ህዝበ ውሳኔ ባላደራጀ ጊዜ እንዴት ይፈፀማል? የሚለው ጥያቄ ነው። ከህገመንግሥታችን ላይ ለመመልከት እንደሚቻለው፣ ሪፈሬንደም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይደራጃል፤ በአብላጫ ድምጽ ጥያቄው ከተደገፈ፣ የጠየቀው ህዝብ ክልል በመሆን አዲስ የፌዴሬሽን አባል ክልል ይሆናል፣ እኩል ሥልጣንና ተግባራት ይኖሩታል ከሚለው ውጭ ህገመንግሥቱ ያለው ነገር የለም። ይሁንና ህገመንግሥቱ ዝም አለ ማለት መፍትሄ የለም ማለት አይደለም።

በህገመንግሥቱ የአተረጓጎም መርህ/rules of constitutional interpretation/
----------------------------------------------------------------------
ለዚህም የህገመንግሥቱን ተቀዳሚ ተልዕኮና: በተጠቀሰው አንቀጽ ሥር ጉዳዩን በጥንቃቄ ያየበትን መንገድ ማጤን ተገቢ ይሆናል። ይህንን የሚናገኘውን በህገመንግሥቱ የአተረጓጎም መርህ/rules of constitutional interpretation/ ውስጥ ነው። እንደሚታወቀው ህገመንግሥት በባህሪው አጠቃላይ/ generality እና አጭር ነው። ቁልፍና ምሰሶ የሆኑ ጉዳዮችን በመደንገግ ሌሎች የህገመንግሥቱን ተልዕኮና ዓላማ መሠረተ ባደረገ መልኩ በትርጉም እንድሟሉ ይደረጋል። በዚህም መሠረት ህዝበውሳኔ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ባልተደራጀ ጊዜ ምን ይፈፀማል የሚለውን በዚሁ የህገመንግሥቱ መንፈስ/spirit of the constitutional/ ውስጥ ሆነን ማየት እንደምኖርብን የህገመንግሥት አተረጓጎም መርህ ያስገነዝበናል።

ከዚህም ስንነሳ፣ ህገመንግሥቱ የህዝቦች የስምምነት ቃልኪዳናቸው ነው። “ጥያቄዬንና ፍላጎቴን ያንፀባርቃል፣ ጥያቄዬ በዚሁ አግባብ ይስተናገዳል” ብለው ህዝቦች እንደማሰሪያቸው አድርገው ያፀደቁት ብቸኛ የመተማመኛ ሰነድ ነው። በዚህም የተነሳ፣ ህገመንግሥቱ ለህዝቦች ጥያቄ፣ በተለይም የራስን ዕድል በራስ የመወሰንና የራስን መንግሥታዊ መዋቅርን የመመሥረት ጥያቄ/the right to self-determinationa and self-administration/ ለድርድር የምይቀርብ፣ በአደጋ ጊዜ እንኳን የማይታገድና በማናቸውም ሁኔታ ተፈጻሚ የሚሆን ነው ብሎ አስቀምጦታል። ይህ መገንጠልን/seccession/ ጭምር የሚያካትት ነው። ከዚህ ተነስተን ስናይ፣ የራስን ክልል የመፍጠርን አስፈላጊነት ህገመንግሥቱ ለክርክር የሚጋለጥ አለመሆኑን አምኖ በተበጀው ህገመንግሥታዊ መስመር ምላሽ እንዲያገኝ ታሳቢ አድርጓል። በመሆኑም በቀላሉ የሚታይና የሚታለፍ አለመሆኑን መገንዘብ ይገባናል።

ሁለተኛውና መሠረታዊው ነጥብ፣ በአንቀጽ 47 ሥር ህገመንግሥቱ የዘረዘራቸውን አስፈላጊ ቅድመሁኔታዎች ማየት ነው። ይህንን በጥንቃቄ በምናይበት ጊዜ፣ በክልል ጥያቄ ዙሪያ አብዛኛው ሚና ጠያቂውን ህዝብ/people concerned/ የሚመለከት መሆኑን ነው። ጥያቄ ማቅረብ፣ በሁለት ሶስተኛ አጽድቆ ለክልሉ ማሳወቅ የሚለው ነው። እነዚህ ጉዳዮች በክልል ጥያቄ ላይ መሰረታዊና ዋና ምሰሶች/fundamentalls/ ናቸው። ይህንን በህግ አነጋገር መሠረታው መብት (substantive rights) የሚንለው ነው። የቀረው ሪፌሬንደም ማደራጀት ነው። ይህ ደግሞ በክልሉ ምክር ቤት የግዴታ የሚፈፀምና ህገመንግሥቱም ምክር ቤቱ እንዲፈጽመው በግዴታ መልክ የደነገገው ጉዳይ ነው።

የክልሉ ምክር ቤት ህዝበ ውሳኔ ያደራጃል ብሎ ሲያስቀምጥ እንደሁኔታው ሊያደራጅም ላያደራጅም ይችላል በሚል በቀላል አገላለጽ ኣላስቀመጠም፣ በግዴታ መልክ በአንድ ዓመት የጊዜ ገደብ ውስጥ ፈጽም ብሎ በግዴታነት አስቀምጧል። ይህ ሁሉ የሚያሳየው፣ የህገመንግሥቱ ፍላጎት የህዝቦችን ጥያቄ መደግፋና አግባብ ምላሽ እንድያገኙ ዝግጁ መሆኑን ነው፣ የመንግሥትን ቸልተኝነት ወይም አላስፈላጊ ጠልቃገብነትንም ለመቆጣጣር ያስቀመጠው ልጓም ነው። 
በሠረታዊ መብትና የሥነሥርዓት ድንጋጌዎች መካከል ያለው ቅራኔ እንዴት ይፈታል?
------------------------------------------------------------------------
ቀጥሎ የቀረው ህዝበ ውሳኔ ነው። ህዝበ ውሳኔ ከዋናው መብት ጋር የሚነጻፀር አይደለም። የመጀመሪያ በሁለት-ሶስተኛ (2/3rd) ድምጽ ድጋፍ በዞን ምክር ቤት አስወስኖ ለክልል ማሳወቅ የሚለው መሠረታዊ መብት (substantive right) ነው። ህዝቦች የሞቱለትን ዓላማ የሚያረጋግጡበት መሠረታዊ ነጥብ ነው። ከዋናው ጥያቄ ክብደት አንጻር ሲታይ፣ ህዝበ-ውሳኔ ማደራጀት ግን የአካሄድ ወይም የሥነሥዓት ጉዳይ (procedural) እንጂ መሠረታዊ የመብት ድንጋጌ አይደለም። ጉዳዩ የህዝብ መሆኑን፣ የብዙሃኑ ፍላጎት መሆኑን ለማረጋገጥ የተቀመጠ መጠነኛ መመዘኛ እንጂ መሠረታዊ ቁም ነገር ያለው ህዝበ-ውሳኔው ላይ ሳይሆን በጥያቄው ላይ ነው።

ይህንን መፈፀም የሚጠበቅበት ተገቢው አካል፣ ባልፈፀመ ጊዜ፣ ህገመንግሥቱ ምን ታሳቢ አድርጎ ነው ዝም ያለው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። መልሱ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ነው። መሠረታዊ መብትን ጠቅሶ የሚፈጸምበትንና የፈጻሚውን ግዴታ አስቀምጦታል። የጊዜ ገደቡን በአስገዳጅ ሁኔታ አስቀምጧል። ህዝበ-ውሳኔ ባላደራጀ ጊዜ የሚፈፀመውን በግልጽ ቋንቋ ባይናገርም “ባንተ በኩል ያለውን ግዴታ ተወጥተሃል፣ በነሱ በኩል ያለውን አልተወጡም፤ ባንተ በኩል ያለው ጥያቄ መሠረታዊ በመሆኑና የቀረው የአካሄድ ጉዳይ ብቻ በመሆኑ ጥያቄህ ተቀባይነት አግኝቷል” ማለቱ ነው። ይህንን ታሳቢ ባያረግ ኖሮ፣ ወይም ህዝበ ውሳኔ ሳይደረግ ክልል መሆን የማይቻል ቢሆን ኖሮ፣ “ባላደራጀ ጊዜ ይሄ ይሄ ይፈፀማል…” በማለት አማራጮችን ያስቀምጥ ነበር። አላስቀመጠም ማለት ደግሞ በተቃራኒው ሲተረጎም በያዝከው መንገድ ጨርሰው ማለቱ ነው። የህገምነግሥቱ አርቃቂዎችም ይህንን አስቀድመው እንደገመቱት (foreseen) ለማየት ይቻላል።

“ህዝበ-ውሳኔ ባይደራጅ” የሚለውን ሳይጨነቅ፣ አዲስ የሚፈጠረው ክልል የፌዴሬሽን አባል ክልል ይሆናል ማለቱ፣ ሪፈሬንዴም በአግባብ ማካሄድ ባልተቻለ ጊዜ ጥያቄው ድጋፍ እንዳገኘ ታምኖ የፌዴሬሽኑ አባል ክልል ሆነሃል የሚለውን ሃሳብ በሚያጠናክር መልኩ የተቀመጠ ነው።

በዚህም ትርጉም መሠረት አልረካሁም የሚል እንኳን ካለ፣ በህግ አተረጓጎም መሠረት፣ በሥረነገር ህጎች (ዋናውን መብት የሚደነግግ ድንጋጌ, provisions declaring substantive rights) እና የሥነሥርዓት ህጎች (ያ መብት የሚፈፀምበትን አካሄድ በሚደነግግ, provisions stipulating procedure) ህግ መካከል አለመጣጣሚ ቢፈጠር ተፈጻኒ የሚሆነው ዋናውን መብት የደነገገው ድንጋጌ ነው። በያዝነው ጉዳይ ላይ የክልል ጥያቄ ተፈጻሚነት ነው።

ይሄን የሚያክል ህዝብ፣ ፍላጎቱን ገልጾ፣ ህገመንግሥታዊ አካሄድን ተከትሎ አስወስኖ፣ ከዚያም አልፎ መሪሪ ትግል አድርጎ የደም ዋጋ ገብሮ የጠየቀው ጥያቄን፣ የሆነ 3ኛ አካል “ህዝበ-ውሳኔ አላደራጅም ብሏልና ጥያቄህ ውድው ነው” ብሎ ማሰብ ከህገ-መንግሥቱ ዓላማና ተልዕኮ በተቃራኒ መቆም ነው። የሥነ-ሥርዓት ድንጋጌ የሰፈረው ዋናውን ጥያቄ እንዲያስፈጽምና እንዲያፀና እንጂ እንድሸረሽር ወይም ውጤት-አልባ እንዲያደርግ አይደለም። በአንድ ወቅት ወንድሜ አቶ ፍላታ ጊግሶ ሲጽፉ እንዳሉት: በህግ አተረጓጎም መርህ ውስጥ ህጎችና መብቶች ዋጋ እንዲኖራቸው ተደርጎ ይተረጎማል እንጂ ውጤት አልባ እንዲሆኑ ተደርገው አይተረጎሙም።

ማጠቃለያ፤
-----------
በመሆኑም፣ የህገመንግሥቱን ዓላማ፣ የብሄሮች ጉዳይና ተያያዥ የክልል ጥያቄ በህገመንግሥቱና በፌዴራል ሥርዓቱ የተሰጠውን ልዩ ክብደት፣ እንዲሁም ሪፌሬንዴም የሚያደራጀው አካል በምን ጊዜ ውስጥ መፈፀም እንዳለበት የሚለው ተለክቶ መቀመጡ ህዝበ-ውሳኔ ባልተደራጀ ጊዜ “ጉዳዩ ተጠናቅቋል፣ በራስህ ክልልነትን ማወጅ ትችላለህ…” የሚለውን በግልጽ ያሳየናል። 
በመሆኑም፣ የሚሊዮኖችን ጥያቄ፣ ሺዎች የሞቱለትና የቆሰሉለት ጥያቄ ሪፌሬንዴም ባልመደራጀቱ ወደኃላ ይመለሳል የሚለው የህገመንግሥቱ ዓላማና ድንጋጌ ባለመሆኑ፣ የቀረውን የቤት ሥራ በፍጥነት በማጠናቀቅ የራስን ክልል ማደራጀትን ህገመንግሥቱ ስለሚደግፍ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ቆርጠን እንነሳ እንላለን።

ህገመንግሥቱ ህልውናና ትርጉም የሚኖረ ገዥዎች ሲጥሱ አሜን በማለት ሳይሆን በችግር ወቅትም ቢሆን በንቃትና በትጋት በመቆምና በመተግበር ነውና። በግልጽ ያልተብራሩ ጉዳዮች ላይ አጠር እያደረግን ለ አንባቢዎቻችን የምንገልጽ ይሆናል።

ህዝበ ውሳኔ ሲዘገይ በራስ የማወጅ ጊዜው ግን ቅርብ መሆኑን እንወቅ።
ድል ለሰፊው ህዝብ

ጤና ይስጥልኝ።

ኪንክኖ ኪኣ