Gudumaale

   Sidaamu Daga Budu Battala
Connecting Sidama People

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከሲዳማ ህዝብ ጋር ዳግም ለስብሰባ: አስፈላጊነቱና የሚያሳድረው ጥርጣሬ 


© ኪንክኖ ኪአ

እንደመንደርደሪያ
==============
በጥቁር አፍሪካ ማርክስስታዊ የአንባገነን ሥርዓት አስፍኖ በሃገራዊ አንድነት ሰበብ በርካቶችን ህይወት የቀጠፈው ደርግ የተገረሰሰው የተለያዩ ብሄሮችና ብሄረሰቦች የነጻነት ታጋዮች በከፈሉት በመራር ትግል ነው። ትግሉ፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚኖሩትን በርካታ ህዝቦችን ባህል፣ ማንነት፣ ቋንቋና የፖለቲካዊ ፍላጎትን ማስተናገድ የተሳናትና የተወሰነው ቡድን ብቻ በበላይነት የሚዘውራት አገር የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ የማያንፀባርቅ በመሆኑ ይሕንኑ መንግሥታዊ አቀራረብ/state approach/ በመቃወም የተደረገ ነው።

ደርግ ሲገረሰስና አዲስ ፌዴራላዊ ሥርዓት ሲመሰረትም ሁለት ዋና ዋና ቁምነገሮችን አሳይቷል። አንደኛው፣ ኢትዮጵያ በውስጧ ያቀፈቻቸውን በርካታ ህዝቦችን ማንነትና የፖለቲካ ፍላጎቶቻቸውን አጣምራና አቻችላ ለሁሉም የሚጠቅም የፖለቲካ አቋም/state thinking/ ካልያዘች እንደሀገር የመቀጠል ህልውናዋ አደጋ ላይ የወደቀ መሆኑን አሳይቷል። ኢትዮጵያ #እንደዩጎስላቪያ ትበታተናለች ተብላም ተፈርታ የነበረበት ወቅት እናስታውሳለን።

ሁለተኛው ቁምነገር፣ ለዘመናት በማዕከላዊነትና በበላይነት/centralist and supremacist/ አስተሳሰብ የሌሎችን ብሄሮችና ህዝቦች ፍላጎቶችን አፍኖናን የተወሰነን ወግኖች ማምንነትና የፖለቲካ አስተምህሮ የሁሉም ኢትዮጵያ በማድረግ የፖለቲካ እሳቤ ላይ የተመሰረተው የአገሪቱ ፖለቲካ/political foundation basedo n dominant group/፣ ወደጠርዝ በተገፉ ክልላዊ ኃይሎች ሊፈታተንና በመጨረሻም ልሸነፍ እንደሚችል አሳይቶናል።

በዚህ ሂደት የተፈጠረው የፌዴራል ሥርዓት ለዘመናት ደም ላፋሰሱ የማንነት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ሞክሯል። እንደበፊቱ ኢትዮጵያ ያንድ ኃይማኖት፣ ያንድ ባህልና ቋንቋ ብቻ የሚነገርባት etc..የሚባለው ያረጀ ፍልስፍና በመርህ ደረጃ ተነስቶ፣ ኢትዮጵያ የብሄሮችና የህዝቦች አገር መሆኗን፣ በውስጧ የሚኖሩ ህዝቦችም የራሳቸውን መብት በራሳቸው የሚያስከብሩ፣ እንደቀደመው ዘመን እንደሆነ ክብር እንደማይገባቸው ሳይሆን የራሳቸውን ማንነታን አኩሪ ታሪካቸውን የሚንከባከቡና የሚያሳድጉ የፖለቲካ አካላት/able and worthy political entities/ እንዲሆኑ እውቅና የሰጠ የፖለቲካ ሥርዓት በመርህ ደረጃ ለመዘርጋት ተሞክሯል።

ይህ ሥርዓት ያስቀመጠው መርህ፣ የጭቁን ህዝቦችን የፖለቲካዊ ፍላጎት ያንፀባረቀና አፋኙን ሥርዓት የመገርሰስ ተስፋን ያሰነቀ የነበረ ቢሆንም በርካታ ጥያቄዎችን ሳይፈታ አልፏል። በርካቶች ይህንን ሲተቹም የአንዱ የሰሜን የበላይነት በሌላው ሰሜናዊ የበላይነት ተተካ እንጂ የአቢሲኒያው የፖለቲካ አስተሳሰብ ባለበት ነው ከሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።

ይህ ሥርዓት ካልፈታቸውና፣ የሥርዓቱ ኢፍትሃዊነት ጎልቶ ከሚታይባቸው ጉዳዮች ውስጥ ዋነኛው የሲዳማ ህዝብ የክልል ጥያቄ ጉዳይ ነው። የኢህአዴግ ሥርዓት ከመመሥረቱ አስቀድሞ ረዘም ላለ ዘመን ለማንነቱና ለብሄራዊ ክብሩ የተደራጀ የወታደራዊ ትግል አካሂዷል። ደርግን አብዛኛውን የሲዳማ ቀጠና ነጻ ያወጣ ትግል አድርጓል።

ትግል የመገንጠል፣ ወይም ኢትዮጵያን ለመበደል የሚደረግ ሳይሆን በኢትዮጵያ መንግሥትነት ስም ህዝቦችን ያዋረደና ለባርነት የዳረገን ሥርዓት በመደምሰስ ሁሉንም ህዝብ በእኩልነት የሚያይ ሥርዓትን ለመፍጠር የሚደረግ ነው የነበረው። በሽግግሩ ወቅት ለአጭር ጊዜ የተሰጠው የሲዳማ ክልል ያለህዝቡ እውቅናና ስምምነት በኃይል ፈርሶ ደቡብን በማቋቋም ተደመደመ። ይህምም ለሌላ ለተራዘመ ትግል የዳረገ ሆኖ ሰንብቷል። በርካታ የሰው ልጅ ዋጋዎችን አስገብሯል።

በ1997 ዓ/ም ገፍቶ በመጣው ህዝባዊ ጥያቄ መሠረት የሲዳማ ዞን ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ አጽድቆ ለክልሉ መንግሥት አስተላልፏል። መክር ቤቱም የጥያቄውን ህገመንግሥታዊነትና ተገቢነት ተቀብሎ ለህዝበውሳኔ ሲዘጋጅ የአንባገነኑ መሪ መለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ብቅ በማለቱና ጠልቃ በመግባቱ ጥያቄው ፍሬ ሳያፈራ ተንጠልጥሎ ሊቀር ተገዷል። ይህም ይሁን እንጂ፣ ትግሉ ለአፍታም ሳይቆም አሁን እስካለንበት የፖለቲካዊ ክስተት ድረስ ዘልቋል።

የሲዳማን ጥያቄ ዳግም ማጽደቅና ያለፈባቸው መንገዶች..
___________________________________
በ አጭሩ፣ የሲዳማ ዞን ምክር ቤት በድጋሚ በቀን 11/11/2010 ዓ/ም ባደረገው ስብሰባ ጥያቄውን እንደገና በሙሉ ድምጽ አጽድቆ በቀን 13/11/2010 ሪፈሬንደም እንዲደራጅለት ለክልሉ ምክር ቤት ልኳል። የክልሉ ምክር ቤትም የተወሰነ ጊዜን ካባከነ በኃላ በመደበኛ ጉባዔው ተወያይቶ ሪፈሬንዴም ይደራጅ የሚለውን አጀንዳ ተቀብሎ በቀን 12/03/2011 ዓ/ም ህዝበ ውሳኔ እንዲያደራጅ በመጠየቅ ለምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት ልኳል። ከዚያ ወዲህ መንግሥትም ሆነ የምርጫ ቦርድ ምንም ዓይነት ግልጽ መግለጫም ሆነ ውሳኔ ሳይገልጽ ጥያቄው ከፀደቀ እነሆ 9 ወራቶች ተቆጠሩ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይና የሲዳማ ጥያቄ …..
_____________________________________
ጠቅላይ ሚንስትራችን ዶ/ር አብይ ሲመረጡም ሆነ በተደጋጋሚ ወደሲዳማ ከእንግዶቻቸው ጋር ሲመጡ ህዝቡ አስደማሚ አቀባበል አድርጎላቸዋል። ከፍ ያለ ፍቅር አሳይቷቸዋል። በመቀጠልም፣ ዶ/ር አብይ የሲዳማ ጥያቄን ታሪካዊ አመጣጥ፣ የተፈጠሩ ችግሮችን፣ ትግሉ ትውልዶችን የተሻገረ፣ ያለፈና የአሁን ትውልድ ጥያቄ መሆኑን ከሲዳማ ህዝብ ከአዛውንቱ እስከወጣቱ ድረስ ሲያስረዱት ካንደበታቸው ሰምተዋል። የጉዳዩን ታሪካዊነትና ጥልቀት ከዬትኛውም ኢትዮጵያ መሪ ይልቅ በተሻለ ሁኔታ ተገንዝበዋል።

በሀዋሳ ከተማ ከሲዳማ ህዝብ ጋር በነበራቸው ስብሰባም፣ የሲዳማ ህዝብ ጥያቄን የሚመልሱት እሳቸው አለመሆናቸውን፣ ምላሹን የሚሰጠው ህገመንግሥቱ መሆኑን፣ እሳቸው የሚያደርጉት ነገር ቢሆን ኖሮ እዚሁ አደራሽ ውስጥ ፈርመው እስከመሄድ ድረስ በጉዳዩ ማመናቸውን፣ በመጨረሻም ህዝብ እስከታች ድረስ በየደረጃው ጥልቅ ውይይት እንዲያደርግና ህገመንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ጥያቄው እንዲቀርብ ተማምነው ተለያይተዋል። በተባለው መሠረትም በሁሉም የሲዳማ ቀበሌዎችና ወረዳዎች ሰፋፊ ህዝባዊ መድረኮች ተዘጋጅተው ውይይቶች ተደርገውና ዳብረው በዞኑ ምክር ቤት ጥያቄው ፀድቆ ሊቀርብ ችሏል።

በእርግጥ በዚህ ወቅትም፣ ጠቅላይ ሚንስትር Dr. አብይ ጥያቄው ቢዘገይላቸው የጠሉ አይመስሉም ነበር። ። በየግልም በየስብሰባውም ለማዘግየት ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳብቁ ምልክቶችን አሳይተዋል። የተለያዩ ቡድኖች፣ የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ የእሳቸውን የለውጥ ጉዞ የሚያደናቅፍ እንደሆነ አድርገው ሊያሳምኗቸውና የሲዳማን ህዝብ ጥያቄ በተለመደው መንገድ በገሃድ ውድቅ እንዲያደርጉ ሲወተውቷቸው ቆይተዋል።

መረጃዎች አሉ። በዘውገኝነት፣ በጠባብ ብሄርተኝነት በመፈረጅም በዶ/ር አብይም ፊት ሆነ በመላው ኢትዮጵያ ህዝቦች ዘንድ ጥያቄው የተበላሽ መልክና ገጽታ እንዲኖረው ጊዜ ወስደው የሠሩ አካላት አሉ። ይህም ክስትተ አሃዳውያንንና የደኢህዴንን ካድሬዎችን ያላቻ ጋብቻ እንዲፈጽሙ ያስገደደ ነበር። ይህንንም በወቅቱ ጽፈን ነበር። ደኢህዴን አጀንዳ ይፈጥራል፤ ዕድሉና አቅሙ ያላቸው የአሃዳውያኑ አፈቄላጤዎች ህዝቡን በመፈረጅና ሰላማዊ ጥያቄውንና ትግሉን ሲያጥላሉ ተጠምደው አሳልፈዋል። ካሻቸው ደግሞ የሲዳማን ጥያቄ ሲያታጥሉ፤ የሚሊዮኖችን ጥያቄ ሲያጥላሉ “የሃዋሳ ከተማ እታ ፈንታ ምን ይሆናል” ሲሉ ለቆርቆሮና ለህንጻ ሲጨነቁ ታዝበናል።

ይህም ለዶ/ር አብይ መልካም ዕድልን የፈጠረ ነበር ብሎ ለመውሰድ ይቻላል። በመርህ ደረጃ ዶ/ር አብይ የሲዳማን ጥያቄ የሚፀየፉበትና በጠላትነት የሚቆሙበት መሠረታዊ ምክንያት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም። ነገር ግን በሁለት ምክንያቶች ጥያቄውን አይደግፉትም፤ አይፈልጉትም። ቢቀበሉትም ቢዘገይ ጥሩ እንደሆነ ይገምታሉ። አንደኛው፣ ሥልጣናቸው አጥብቀው እስከሚይዙና አስተዳደራቸውን እስከሚያጠብቁ፣ ደቡብ የተባለው እሥር ቤት ሲፈርስባቸው አደጋ እንደሆነ ይገምታሉ። በሁለተኛ ደረጃ፣ አሁን እየሄዱበት ያለው መንገድና ያለውን የፌዴራል ሥርዓት በአሃዳዉያኑ አረዳድ የተቃኘ አረዳድ ስለሚታይባቸው ፌዴራል ሥርዓቱንና የክልሎችን አደረጃጀትም ማፍረስ/reconfiguring state along unitarist visions/ ዓላማ ያላቸው ይመስላሉ።

በዚህም መሠረት፣ “ነባሩ ክልል አደረጃጀትም ችግር ያለበት ነው፣ ለእናንተም ይሄው አይገባችሁም…በአንድ ላይ ተጠንቶ ዘላቂ የሆን ምላሽ ይሰጣል፤ እስከዚያ ታገሱ” የሚል ውስጣዊ እምነት እንዳለ ለማየት ይቻላል።
በነዚህ ጉዳዮችና፣ ሌሎችም አገራዊ የፖለቲካዊ ሁኔታዎችን አስታክኮ የሲዳማ ህዝብ \ጥያቄ ቢዘገይላቸው የሚጠሉበት ምክንያት አይኖርም፣ እሳቸውም የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅመው ይሕንን ሊያደርጉ ይችላሉ። አንዱ የዚህ ማሳያ፣ የተለያዩ የሥራ ማቆም አድማዎች፣ ሚሊዮኖች የተሳተፉበት የተለያዪ ሠላማዊ ሰልፎች በሲዳማ ምድር ሲካሄዱ መንግሥት ጆሮ ዳባ ልበስ ማለቱ ነው። እንደመንግሥት በሠላማዊ መንገድ ለሚጥየቁ ጥያቄዎችና ለሚቀርቡ ቅሬታዎች መግለጫና የመንግሥትን አቋም ማንፀባረቅ ሲገባ ዝም ማለት የህዝቡን ጥያቄና ቅሬታው እንደመናቅ ተድርጎ ሊተረጎም የሚችል ነው። ይህም ከፍ ወዳለ ፖለቲካዊ ቅሬታና ቁጣ ሊቀየር የሚችል ድርጊት ነው።

በሁለተኛ ደራጃ ሊጠቀስ የሚችለው፣ አንድ ሚሊዮን የሚሆን የሲዳማ ህዝብ በተሳተፈውን ህዝበ ውሳኔ ይደረግልን በሚለው ሰልፍ ምክንያት ጉዳዩ ለምን እንዳልተፈፀመ የተጠየቁት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ የሰጡት የሚያበሳጭ ምላሽ አንዱ የመንግሥት አቋም ማሳያ ነውነው። “ለሲዳማ ህዝብ ህዝበውሳኔ ለማደራጀት ጊዜ የለንም። በሌላ ሥራ ተጠምደናል። ይደረግ እንኳን ከተባለ ከመጪው ዓመት ምርጫ በኃላ የሚታሰብ ይሆናል…” ብለው ከሀገሪቱ መሪ ጋር በመናበብ የያዙትን የጋራ አቋም ግልጽ ያደረጉበት ነው። ባጠቃላይ፣ ብዙ ዝርዝሮች ውስጥ መግባት ሳይስፈልግ፣ የዶ/ር አብይ መንግሥት፣ ደግ ደጉን እየተናገሩ ጥርጣሬዎቹን ግን ባሉበት ሆነው፣ ለዚሁ ቀን በቅተናል።

ሰሞነኛ የስብሰባ ጥሪ….
____________________________
ከፍ ሲል በወፍ በረር እይታ፣ የጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ መንግሥት የሲዳማን ጥያቄ ቢቻል ለማስቀረት ካልተቻለም በተለያየ ዘዴ ለማጓተት ፍላጎቱ ያለው መሆኑንና ተግባር ላይም እየዋለ እንደሚገኝ አንስተናል። የአንድን “ባልድረሳ ምክር ቤት ነኝ” ብሎ ለሰየመ ግለሰብ መግለጫና ማብራሪያ የሚሰጠው መንግሥታችን፣ ለዚህ ህዝብ ታሪካዊ ጥያቄ ምላሽ ነፍገው፣ ለመቀልበስ ከሚሠሩ ኃይሎች ጀርባ ቆመዋል በማለት የሚያስጠረጥራቸው ተግባር የህዝቡን ጥያቄ ዝም ማለታቸው ለጉዳዩ የሰጡትን አናሳ ግምት ያሳያል። ይህም በህዝቡ ውስጥ ምን የተለየ ይጠበቃል እንዲል ሊያስገድ ደው ይችላል። ደርድም አፍኖት የኖረው ጥያቄ ነው። ኢህአዴግም በወረቀት ጽፎ በተግባርየ አፈሙዝ ምላሽ ሲሰጥበት የኖረው ጉዳይ ነው። ዶር አብይ ለዚህ ታሪካዊ ጥያቄ ታሪካዊ ምላሽ ቢሰጡ በትውልድ መካክለ የማይጠፋ አኩሪ ታሪክ ጽፈው እንደሚያልፉ እሙን ነው። (ዶር አብይ የሲዳማን ጥያቄ በወቅቱ አልመለሱም ብዬ የማቀርበው ትችት ሌላ የተሻለ ሥራ አልሠሩም ለማለት አይደለም)።

አሁን ህዝቡ ህዝበ-ውሳኔ እንዲደራጅለት አጥብቆ እየጠየቀ፣ ከግራም ከቀኝም የሚያጋጥም ፈተናዎችን በትዕግሥት እየተከላከለ ቆይቶ፣ አሁን በመንግሥት እርምጃ ላይ ተስፋ ቆርጦ በራሱ መንገድ እልባት ለመስጠት እያሰበ ባለበት ሰዓት ላይ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለውይይት ህዝቡን መፈለጋቸው መግፍዔው ምን ይሆን ብለን በጥርጣሬ እንዲናይ ያደርገናል። የመረጃ ምንጮች እንደሚያሳዩት ከሆነ ሪፈሬንዴም ለማካሄድ መንግሥት ፍላጎት የለውም፤ በራሱ ሥልጣናዊ ሥራ የተጠመደ ይመስላል። በዚህ ላይ የምርጫ ቦርድ አሁን ባወጣው መግለጫ ለሲዳማ ህዝብ ህዝበ-ውሳኔ ለማደራጀት ተገቢ ዝግጅት አላደረኩም ብሏል። ይህ መግለጫ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሲዳማ ህዝብ ጋር ለመወያየት በፈለጉበት ወቅት ላይ የተሰጠ ነው። አላማውም፤ ህዝቡ አስቀድሞ ህዝበውሳኔ እንደማይካሄድ አዝማሚያውን አውቆ እንዲቀመጥ መልዕክት ለመስደድ የታለመ ይመስላል።

የስብሰባው አግባብነት፤
___________________________________
እንግዲህ ዴሞክራሲያዊ በሆነ አስተዳደርና አካሄድ መሠረት ውይይቶችን ማድረግና መነጋገር ጉዳዩን በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ሁነኛ መንገድ ነው። በዚያ ላይ የአንድ አገር መሪ ከሚፈልገው የህብረተሰቡ ክፍል ጋር እወያያለሁ ጉዳይ አለኝ ካለ ለምን ትወያያለህ ሊባል አይገባም። ነገር ግን አስፈላጊነቱና ዓላማውን መቃወምና ሂስ ማድረግ ዴሞኪራሲያ አካሄድ ነው።

ጥያቄው ህገመንግሥታዊ አካሄዶችን አጠናቅቆ አፈፃፀም ብቻ በቀረው ጉዳይ ላይ እንደገና ከእናንተ ጋር ሊወያይ የሚለው ፍላጎት ከመልካም ፍላጎት የመነጨ ነው ብሎ ለመቀበል ያስቸግራል። በርካታ ተቃውሞዎችና ለመንግሥት ጥሪዎች ሲደርሱ መንግሥት ዝምታን መርጦ በህመንግሥቱ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ የሚደረግ ጉባዔ ጥያቄውን ከመፈጸም ፍላጎት ይልቅ የማዳከም አዝማሚያ ያለው መሆኑን መመልከት ይቻላል። መነጋገር ቢያስፈልግ ቀደም ብሎ በቂ ጊዜ እያለ ነበር። ይህንን ፍልጎቱን የሚያሳዩ ሌሎች ጉዳዮም አሉ።

ምን ምን ጉዳዮች ሊነሱ ይችላሉ?
___________________

አሁን ምናልባትም ምን ምን ጉዳዮን ታስበው ነው ስብሰባው የሚጠራው? የሚለውን ቢናይ የተለያዩ ሃሳቦችና ማታለያዎች ሊቀርቡ ይችላሉ። ለአብነት ሊገመት የሚችለው፣ ህዝበ-ውሳኔ እንዲዘገይ የሚለው ሊነሳ የሚችል ነው። መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ “ሪፌሬንዴሙ መካሄዱ አይቀርም ነገር ግን ጊዜ ማራዘም አስፈልጓል” የሚለው በውስጥ መስመር እየተሰራበት ነው።

ለዚህም እንደ ምክንያት ሊቀርቡ የሚችሉት፣ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ፣ አስፈላጊ ጥናቶች አለመጠናቀቃቸው፣ ሲዳማ ክልል ሆኖ ሲወጣ የሌሎች ህዝቦችን ዕጣ ፈንታ አስቸጋሪ ስለሆነ ጉዳይ ተጠንቶ አቅጣጫ እስከሚቀመጥ ትንሽ ጊዜ ታገሱ የሚለው ጎልቶ የሚወጣ ይመስላል። ለዚህም ሞራላዊ ጫና ለመፍጠር እንዲረዳ፣ ለኢትዮጵያ ሠላምና ትንሳኤ አብዝተን መጨነቅ እንዳለብን፣ ክልል ዬትም አይሄድም ግን አገራዊው ለውጥ መልክ እሰከሚይዝ መተባበርና ጥያቄያችንን አፍነን መያዝ እንዳለብን ሊነገረን ይችላል። ካልሆነም በእኛው በኩልም ዝግጅቱ አልተጠናቀቀምና ለሌላ ችግር እንዳንጋለጥ ሊመክሩንም ይችላል።

ቀደም ሲል አቶ መለስ እንዳደረጉትም፣ የሲዳማ ሽማግሌዎች ጉዳይን ለጥቂት ጊዜ አደብ እንዲያስገዙ ተማጽኖ ሊያቀርቡም ይችሉ ይሆናል፤ በዚህ አካሄድ የመቀልበስ ልምዱ ስላለ። ሌላው የሚታየኝ ጭላንጭል፣ ሌሎች ወዳጅ አካላትንና ሽማግሌዎችን አቅርበው ህዝብ ለህዝብ ውይይት መልክ በማስያዝ ሌላው ህዝብ በለውጡ ሰበብ ጣልቃ እንዲገባም በማድረግ ለማርገብ ሊታሰብ ይችል ይሆናል።

እና ስብሰባውን የሲዳማ ህዝብ መሳተፍ አለበት??
____________________________
መልሱን ለህዝቡ መተው ነው። ነገር ግን ከውይይቱ የሚገኘው ጥቅም ብዙም አይታይም፣ ይልቅ ጉዳቱ ጎልቶ ይታያል። በ 97 ዓ/ም ለፍጻሜ ከጫፍ የደረሰው የክልል ጥያቄ በእንዲህ አይነት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር በተደረገ ውይይት ከሽፏል። ግማሹ ተሳታፊን በተጽዕኖና በማስፈራራት ወይም በመደለል በማሳመን፣ የተስማማውን ባልተስማማው ላይ በማነሳሳት ልዩነትንና አለመተማመንን ለመርጨት ደኢህዴንም ተግቶ እንዲሠራ የተሻለ ዕድል ይፈጥርለታል። ከሁሉ በላይ ግን፣ “ተቀዷል …ዋጋ የለውም” ተብሎ ካልሆነ በስተቀር ህገመንግሥቱ ለእንደዚህ ዓይነት ውይይቶች ቦታና ዕድል አልሰጠም። ክልል ለማግኘት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ሽማግሌዎችና ሴቶች ይደራደራሉ አላለም። ህገመንግሥቱ አይሠራም ብለው በግልጽ ቋንቋ ከተናገሩ፣ ከዚያ በኃላ የትግሉን መልክ የሚወስን ይሆናል።

በመሆኑም ውይይት ማድረግና አለማድረግ የመላው ህዝብ ምርጫና ውሳኔ ሆኖ፣ በውይይት ከህገመንግሥቱ አካሄድና አፈጻፀም ዝንፍ ለማድረግ ከተሞከረ ተቀባይነት እንደሌለውና ህዝባችንን የማይወክል መሆኑን ለማሳየት ነው። ኤጄቶ በህግና በፖለቲካ ተደራጅቶ የሚንቀሳቀስ ሳይሆን ህዝባዊ ስብስብ እስከሆነ ድረስ ለብቻው ተለይቶ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር የመደራደርና የመወያየት ዓላማም አሠራረም ሊኖረው አይችልም።

ህገመንግሥታዊ ጥያቄያችን ይከበር!!